በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፐብሊክ ሰርቪስ የሰው ሀብት ልማትና ሥራ አመራር ዘርፍ
በሰው ሀብት ልማትና ስራ አመራር ዘርፍ ከሚከናወኑ በርካታ ተግባራት ውስጥ ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ይገለጻሉ፡-
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የሰው ሀብት ልማትና ስራ አመራር ዘርፍ ውስጥ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የሰው ሀብት ሕጎች አተገባበር እና የኢንስፔክሽን ሥራዎችን ጠንካራና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በክልሉ ከተደራጀበት ጊዜ አንስቶ የክልሉን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት አድርጎ በተዘጋጁት የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ፤ ደንብና መመሪያዎችን ወደ ሚተገበሩበት ቦታ በማድረስ አፈጻጸማቸውን ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ተግባር ተሰርቷል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የሰው ሀብት ህጎች ኢንስፔክሽን ስራዎች አተገባበርን በማጠናከር እና የአሰራር ስርዓቱን መነሻ አድርጎ በተከናወኑ ስራዎች የተፈጸሙ ጥሰቶችንና ህገ ወጥ አሰራሮችን በመለየት ግኝቶችን መሰረት አድርጎ ብልሽቶችና ህገወጥ አሰራሮች በማረም የባከነ የመንግስት ሀብት ማስመለስና ሊባክን የነበረ የመንግስትና ህዝብ ሀብትና ገንዘብ እንዳይባክን ማድረግ የሚያስችል ተግባር ተከናውኗል፡፡
የሰው ሀብት ልማትና አቅም ግምባታ ተግባራት አፈጻጸምን ከማሻሻል አንጻርም በዘርፉ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ሆኖ በርካታ ክልላዊና አገራዊ ዕድሎችን በመፍጠር የአቅም ግምባታ ስራዎች ከመሰራታቸውም ባሻገር ለአመራሩና ለሰራተኛው የአጭርና የረጅም ጊዜ የትምህርትና ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ለማድረግ የማመቻቸት፣ የመደገፍና የማስተባበር ሥራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ እነዚህም የአቅም ግምባታ ስራዎች ውጤታማና ስኬታማ እንዲሆኑ ማድረግ በመቻሉ በክልሉ የመንግስት ሰራተኞች እና አመራሮች ውጤታማነት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ መነሳሳትንና ውጤታማነትን ማሳደግ ተችሏል ፡፡
በዘርፉ በመከናወን ላይ ከሚገኙ ተግባራት መካከል አንዱ አዲሱ የነጥብ የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ስነዘዴ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ የማድረግ፤ የክፍያና የጥቅማጥቅም ሥርዓቱ በአሰራር መሰረት እንዲከወን ማድረግና ሰራተኛውም በስራው ተነሳሽነት እንዲፈጥር ማድረግ ያስቻለ ተግባር ነው፡፡
በሌላ መልኩ የመንግስት ተቋማት የአዳረጃጀት ውጤታማነት ጥናት እንዲካሄድ የማድረግ እና ውጤታማ የአደረጃጀት ማሻሻያዎች በአሰራር ስርዓት ታግዘው ተግባራዊ እንዲደረጉ ማስቻልም ተጠቃሽ ነው፡፡ ስለሆነም ለስራው ስኬታማነት ተከታታይነት ያለው ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በሒደቱም ጠንካራ መንግስታዊ ተቋማት እንዲፈጠር የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በአዲሱ ክልል የተደራጁ ተቋማትን ብቃት ለማሳደግ የሚሰራው ስራ በተቋማቱ ውስጥ ስራቸውን በብቃት፣ በተነሳሽነት፣ በጥራትና በጊዜ ማከናወን የሚችሉ ባለሙያዎችን ለመፍጠር አስችሏል፡፡
በዘርፉ ከሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ አንዱ የሆነውን በሰው ሀይል ስምሪቱ ረገድ ያሉትን ጥንካሬዎችና ጉድለቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የመለየት ስራ ሲሆን በብቃት ላይ የተመሰረተ፣ ጥራት ያለውና በተባለው ጊዜ ስራን ማከናወን የሚችል አገልጋይ የሰው ሀይል እውን ለማድረግ እንዲያስችል ከተለያዩ የጥናት ኢንስቲቲዩቶችና የአመራር ጥናት አካዳሚዎች በተወጣጡ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት አማካይነት ሳይንሳዊ የሆነ ጥናት ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በሰው ሀይል ስምሪት ጥናት ላይ ተመስርቶ በሚሰራ ስራ በክልሉ በማገልገል ላይ ያለውን የሰው ሀይል ስምሪት የሚፈለገው ውጤት እንዲያስገኝ ሆኖ እንዲከናወንና እንዲመራ ማድረግ የማስቻል ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ሌላው የክልሉ የሰው ሃብት ስራ አመራር፣ የመረጃ አያያዝና አደረጃጀት ሥርዓት እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ የተጀመረውን የመንግሥት ሠራተኞች መረጃ ዲጂታላይዝድ (ስካን) በማድረግ አግልግሎቱን ከወረቀት ንክኪ ነፃ የማድረግ ሥራ በዘርፉ በመከናወን ላይ ከሚገኙ ተግባራት መካከል ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ሥርዓት Integrated Civil Service Management Information System (ICSMIS) ትግበራ ውጤታማ ማስተግበርና ማስቀጠል ስራ ይሠራል፡፡ ለዚህ ስራ ስኬታማነት በዘርፉ የተሻለ ልምድና እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች መለየት፣ በቁሳቁስ የማሟላትና በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ስራን አጠናክሮ ለማስቀጠል የመረጃ ማሰባሰብ፣ የማደረጀትና የተሟላ መረጃ ለውሳኔ የማቅረብ ተግባር በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ክልላዊ የሰው ሀብት መረጃ አጠነቃቀር፣ አስተዳደርና አቅርቦት ስራው በዘመናዊና በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ የበለጠ እንዲዘምን በማድረግ መረጃዎች እንዲሰበሰቡ፣ እንዲጠናከሩና ተተንትነው ለውሳኔ ሰጪ አካላት በሚፈለገው ጊዜና ሁኔታ የማቅረብ ስራ ለማሻሻል መከናወን ያለባቸው ዘመናዊ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ስለሆነም የዘርፉን ሰራተኞች አቅም የማጎልበት ስራ ማከናወን እንዲቻል የረጅም ጊዜ የትምህርት እድል ማመቻቸትና በየጊዜው ከሚመጡ አዳዲስ አሰራሮች ጋር በፍጥነት ተላምደውና ተዋህደው የተቀረውን የሰው ሃይልም መልሰው ማብቃት የሚያስችላቸውን ወቅታዊና ተከታታይነት ያለው የመረጃ አደረጃጀት ስልጠና የመስጠት ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በዘርፉ በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ከክልል መዋቅር እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ ባለሙያዎችን በዘመኑ በማይታለፈው በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅማቸውን አሳድገው የመረጃ አሰባሰብ፣ አደረጃጀትና ትንታኔ ሰርተው ለውሳኔ ሰጪ አካል የማቅረብ ተግባር ተጠናክሮ የሚተገበር ይሆናል፡፡
በመጨረሻም በሰው ሀብት ልማትና ስራ አመራር ዘርፍ በመከናወን ላይ የሚገኙ ተግባራትን ውጤታማነት የበለጠ ማሻሻል እንዲቻል በየወቅቱ በመገምገምና አስፈላጊ የሆኑ ስራዎችን በተገቢው በማከናወን ጥንካሬዎቻቸውን እና ጉድለቶቻቸውን በተከታታይነት የመለየት ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ስለሆነም የሰው ሀብት ልማት ስራዎቹ በሚከናወኑበት ጊዜ የተለዩ ጥንካሬዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማረጋገጥ ወደ ስኬት ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በዘርፉ ስራዎች ላይ ያሉባቸውን ጉድለቶችን አንጥሮ በማውጣት በእውቀት፣ በአሰራር፣ በክህሎትና በግብዓት አቅርቦት ረገድ የተለዩ ክፍተቶችንና ማነቆዎችን ተረባርቦ መፍታት እንዲያስቻል አስቀድሞ በዕቅድ የማካተት ስራም ይሰራል፡፡ በዚህም መሰረት ለሰው ሀብት ልማትና ስራ አመራር ስራው ስኬታማነት አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን በሙሉ ለይቶ አቅም በፈቀደ ልክ የማሟላትና የማመቻቸት የሰው ሀብቱንና የተቋማትን አቅም የማጠናከር የማጎልበት ቀጣይነት ያለው ሥራ ይሰራል፡፡