Skip to main content
000012

(ሃላባ፦ ነሐሴ /28/2018) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል  ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የ2018  አፈጻጸም እና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ የሚመክር የሴክተር ጉባኤ ''ሰው ተኮር አገልግሎት ለልህቀት'' በሚል መሪ ሀሳብ  በሀላባ ቁሊቶ ከተማ አካሂዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ እንደገለፁት በተቋሙ በተሰሩ የሪፎርም ስራዎች በዜጎች ይስተዋሉ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መቀነስ ተችሏል።

ክልሉ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር ሪፎርም የገቡ ቢሮዎች ማለትም ጤና፣ፋይናንስ፣ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ፣ትምህርት ፣ ገቢዎች እና ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮዎች የዝግጅት ምዕራፍ  ዕቅድ በማዘጋጀት በዌቭ 1 የገቡና የዝግጅት ምዕራፍ እያገባደዱ ስለመሆናቸው ገልፀዋል።

በዌቭ 2 ትምህርት፣ ግብርና፣ ፕላንና ልማት እና ገቢዎች ቢሮዎች የዝግጅት ምዕራፍ ስራቸውን እያጠናቀቁ የሚሄዱ ሆኖ ሌሎች ቢሮዎችም ስትራቴጂውን ተከትለው በዚሁ ዓመት ወደ ሪፎርሙ የሚገቡ ይሆናሉ ብለዋል።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት 7 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመርቀው  ለህዝብ ቀልጣፋና ወጪ ቆጠጣቢ በሆነ መልኩ  ዋና ዋና አገልግሎቶች ለህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

 ተመርቀው አገልግሎት እየሰጡ ባሉ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋይ እርካታ በአማካይ 96 ከመቶ በላይ መድረስ መቻሉን  የጠቆሙት ኃላፊው በቀጣይም የተቀሩ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ወደ መሶብ ማዕከል ለማስገባት በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

በተጨማሪም በ3ተኛ ዙር ለመሶብ አንድ ማዕከል ግንባታ አስር ከተማ አስተዳደሮች የተለዩ ሲሆኑ ከነዚህም የተወሰኑት ተስፈ ሰጭ እንቅስቃሴ እያደረጉ እና ቀሪዎቹ በቅርብ ጊዜ ወደ ትግበራ የሚገቡ ይሆናሉ ብለዋል።

በሀገራችን ለተመዘገቡ ለውጥና ዕድገት የፐብሊክ ሰርቪስ ሚና የላቀ ቢሆንም አሁንም ተልዕኮውን ውጤታማ ከማድረግ አንፃር ክፍተቶች ያሉት በመሆኑ ቅንጅታዊ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል።

ለሁሉም የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅዶች ማስፈጸሚያ ሞተር የሰው ሀይልን አቅም በመገንባት ለህዝብ አገልግሎት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ሲሉ አቶ ገብሬ ተናግረዋል።

በክልሉ ትልቅ ችግር ሆነው የቆየውን ትክክለኛ እና ተአማኒነት ያለው የሰው ሀይል መረጃ አያያዝ ችግርን ለመፍታት በየደረጃው የመንግስት ሰራተኞች እና የስራ ኃላፊዎች መረጃዎችን በሲስተም የማስገባት ስራ እየተሰራ ቢሆንም ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።

አሁንም ቢሆን በየተቋማቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለህዝብ ቅሬታ ምንጭ እንዳይሆን ከተለመደው አሰራሮች በመውጣት ለሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከምን ጊዜም በላይ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአገልግሎት ልህቀት የሆነ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አስገንዝበዋል።

 በበጀት ዓመቱ የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ጉድላቶችን በማረም ህዝቡን በአገልግሎት አሰጣጥ ለማርካት በቀጣይ መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት የህዝብን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በተቋሙ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በክልሉ የተጀመሩ የአንድ ማዕከል መሶብ አገልግሎት ስራዎችን ማጠናከር እና በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆን በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቃል ብለው ለተግባሩ ውጤታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ገልፀዋል።

በመጨረሻም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መዋቅሮች እውቅና እና የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው ሲሆን የሀላባ ቁሊቶ  መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ምልከታም ተደርጓል።