የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት ያለፉት አሥር ወራት የመልካም አሰተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ልየታና አፈታት አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዝግጅት አቅጣጫ ላይ የሚመክር ግምገማ ነክ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መድረክ በዱራሜ ከተማ አካሂዷል።
ግምገማ ነክ የአቅም ግንባታ ሥልጠናው ሴክቶራሊ ለዞንና ለልዩ ወረዳ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ እና ጽ/ቤት የመልካም አስተዳደር የሥራ ሒደት አስተባባሪዎችና ለክልል ተቋማት የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ፎካል ፈጻሚዎች የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የመልካም አሰተዳደር ጉዳዮች ድጋፍና ክትትል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ቢጃሞ እንደገለጹት ያለፉት አሥር ወራት እንደ ክልል የተለዩ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ከመፍታት አንፃር በርካታ ሥራዎች የተሠሩበትና ውጤትም የተመዘገበበት ሲሆን የህዝቡን እርካታ በሚፈላገው ልክ ከማረጋገጥ አኳያ አሁንም ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
እንደ ክልል በሁሉም ደረጃ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን የመፍታት ጉዳይ ቁጥር አንድ አጀንዳ ተደርጎ እንዲሰራ በክልሉ የበላይ አመራር የተቀመጠውን አቅጣጫ መነሻ በማድረግ በሁሉም ደረጀ የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው የተለዩ ችግሮችንም በስድስት ዘርፎች ማለትም በማህበራዊ ልማት ዘርፍ፣ በኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ፣ በመሠረተ ልማት ዘርፍ፣ በሰው ሀብት ልማት ዘርፍ፣ በፋይናንስ ልማት ዘርፍና በህግና አስተዳደር ዘርፍ ለይቶ በማስቀመጥ ችግሮቹን ለመፍታት በተሠራው ሥራ በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን በመጪው የ2019 በጀት ዓመት የተፈቱትንና ምላሽ ያገኙትን በማስፋት ጉድለቶችንና ቀሪ ሥራዎችን ፈጥኖ በማረም በቅንጅት መሥራት ይገባልም ብለዋል።
የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን የመፍታት ጉዳይ የአንድ ጀንበርና በአንድ ወገን ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ችግሮችን ስንለይ የመልካም አስተዳደር መርሆችን ግምት ውስጥ ባስገባና መሳተፍ የሚገባቸውን የህዝብ ክንፍ አካላትን በአግባቡ በማሳተፍ እንዲሁም የተለዩ ችግሮችን ዳግሞ ሊቆጠር በሚችል መልኩ መፍታት እንዲቻል የተለዩ ችግሮችን በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ውስጥ ሊፈቱ የሚገቡ በሚል ለይቶ በማስቀመጥ በትኩረትና በቅንጅት ለመፍታት መሥራት እንደሚገባ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ቢጃሞ አሳስበዋል።
ለመድረኩ በተዘጋጀው የአቅም ግንበታ ሰነድ ላይ ስልጠና የሰጡት አቶ ፍትህአወቅ ፋንታሁን የመልካም አስተዳደር መስፈን ዜጎች በመንግሥት ላይ እምነት እንዲኖራቸው፣ አዎንታዊ አስተሳሰብ እንዲጎለብት፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራር እንዲቀንስ፣ ፍትሃዊ አሠራር እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው የአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲረጋገጥ ሦስቱን የልማት አቅሞች አስተሳስሮና አቀናጅቶ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ሁሉም ተቋማት መንግስታዊ አገልግሎት እየሠጡ ቢሆንም በዚያው ልክ ቅሬታዎች በመኖራቸው የተገልጋይ ቅሬታ ማስተናገጃና ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓቶች ተጠብቀው መፈጸም ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት የዞንና የልዩ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያና ጽ/ቤት የመልካም አስተዳደር ሥራ ሂደት አስተባባሪዎችና የክልል ተቋማት የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ፎካል ፈጻሚዎች አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን በማንሳትና በቀጣይ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ አካል ሆነው ሊሠሩ በሚገባቸው ቁልፍ ተግባራት ላይ መግባባት በመፍጠር በዘርፉ ሃላፊ የስራ መመሪያ እና አቅጣጫ ተሰጥቶ ግምገማ ነክ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መድረኩ ተጠናቅቋል፡፡