Fetehihawek
Wed, 06/03/2026 - 12:54
ወራቤ፣ ግንቦት 26፣ 2018 ዲጂታል አገልግሎትን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ይሰራል አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ከ260 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በዛሬው ዕለት መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በማዕከሉ 6 የተለያዩ ተቋማት 20 አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ጠቁመው፤ በቀጣይ ይበልጥ እየሰፋ ይሄዳል ብለዋል፡፡
ቴክኖሎጂውን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ርዕሰ መስተዳድሩ በከተማዋ ሳምንቱን ሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚችል የገበያ ማዕከልም መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
መንግስት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመፍታት ዲጂታል አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ነው ብለዋል።
ዛሬ በወራቤ ከተማ ተገንብቶ ወደ ስራ የገባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቋት በመስጠት የማህበረሰቡን እንግልት ያስቀራል ነው ያሉት።
መንግሥት ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡