Skip to main content
newa15

ለሪፎርም ተግባራት ውጤታማነት በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባ የምክር ቤቱ የህግና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ። 

(ሆሳዕና፦ ጥር 17 /2018) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል። የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የክልል ተቋማትን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በጽ/ቤቱ እየገመገመ ይገኛል። 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ መሰረት ወ/ሰንበት በግምገማ ወቅት እንደገለፁት ለሪፎርም ተግባራት ውጤታማነት በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል። ከተገልጋዩ ህብረተሰብ ለሚነሱ ቅሬታዎችና ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የፐብሊክ ሰርቪስ አሰራሮችን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል። የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ቅልጣፌ ውጤታማነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ተቋማት በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ በማድረግ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ ውጤታማ ስራዎች መሰራቱ በጥንካሬ ታይቷል ነው ያሉት። 

የሰው ሀብት ህጎች አተገባበር ውጤታማነትን ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አበረታች ናቸው ብለው ለመደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ የኢንስፔክሽን ተግባራት የበለጠ በማጠናከር ህገ ወጥ ተግባራትን መከላከል ያስፈልጋል። በተቋሙ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ወጥ የሆነ አሰራርን እንዲኖር የድጋፍና ክትትል ብሎም አደረጃጀት ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም ገልፀው በተቋምና አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል። 

የክልሉን ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አሰቴር ይርዳው የመልካም አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮቾን በየደረጃው ለመፍታት በተከናወኑ ሰራዎች ጥሩ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው ብለዋል። የመልካም አስተዳደር መርሆዎች ትግበራ፣ የዜጎች ቅሬታ ማስተናገጃና የህዝብ ተሳትፎ ትግበራ በቅንጅት የማጠናከር ስራ ስለመሰራቱም ገልፀዋል። በቀጣይ የታዩ ክፍተቶችን በማረም ለህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል።