ዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችም እንደሚያሳዩት የሰው ልጆች የዕለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የተቆራኘ እየሆነ መጥቷል፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዜጎች ብዙ ውጣ ውረድ ሳያስፈልጋቸው አገልግሎቶችን በቀላሉና ባሉበት ቦታ ሆነው የሚያገኙበትን ሁኔታ አመቻችቷል።
ስለሆነም የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል ኢትዮጵያን 2030 የማሳካትና ቀልጠፋ አገልግሎት የመስጠት ግብ ያለዉ በሀገር ደረጃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የተጀመረ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ(ዶ/ር) ኢንሼቲቭ ነዉ፡፡በፌደራል ደረጃ ከተገነባዉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ልምድ በመዉሰድ በክልላችንም ሞዴል የሆነ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተቋም በሆሳዕና ከተማ ተገንብቶ መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም በክልላችን ፕሬዘደንት ክቡር እንዳሻዉ ጣሰዉ (ዶ/ር) ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
መሶብ የሚለው ቃል አንግሊዘኛ ሲሆን MESOB (Modern Ethiopia Services for Organized Benefits) የአንድ ማዕከል አገልግሎት ይባላል:: ማዕከሉ የኢትዮጵያ ብልፅግና አንዱ አመላካች የሥልጣኔ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በርካታ የተለያዩ ተቋማት ተመጋጋቢ መንግስታዊ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል አሰባስቦ በቴክኖሎጂ በማቀላጠፍ የመስጠት ሂደት ነው፡፡ በመሆኑም የማዕከሉ አገልግሎት አሰጣጥ ተገልጋዮች የሚገጥማቸዉን በርካታ ውጣ ውረድ እና እንግልትን የሚያስቀር፤ ወጪ እና ጊዜን የሚቆጥብ እንዲሁም ብልሹ አሰራር እና ሌብነትን የሚያስቀር ነው፡፡
በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት(ሆሳዕና)
1. ከንግድና ገበያ ልማት ቢሮ፡-አዲስ የንግድ ፈቃድ፣አዲስ የንግድ ምዝገባ፣ንግድ ፈቃድ እድሳት፣ንግድ ምዝገባ ማሻሻያ፣ንግድ ፈቃድ ማሻሻያ፣ንግድ ምዝገባ ምትክ፣ንግድ ፈቃድ ምትክ፣ተመለሽ ፍቃድ በድምሩ 8 አገልግሎቶች፤
2. ገቢዎች ቢሮ፡- የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር
3. ፍትህ ቢሮ ፡-የውክልና ሰነድ ማረጋገጥ፣ ውክልና የመሻር/የመተው ሰነድ ማረጋገጥ፣ የሰነድን ኮፒ ከዋናው ጋር ማመሳከር፣የትርጉም ሰነድ ማረጋገጥ፣የፈቃደኝነት ማረጋገጫ ሰነድ ማረጋገጥ፣የቃለ-መሀላ ሰነድ ማረጋገጥ፣ የውጭ ሀገር ሰነድ መመዝገብ በድምሩ 7 አገልግሎቶች፤
4. ቴሌ፡- ቴሌ ብር አገልግሎት
5. ንግድ ባንክ፡- አካውንት ማውጣት ፣ ሲቢኢ ብር በድምሩ 2 አገልግሎቶች
6. ብሄራዊ መታወቂያ፡- ብሄራዊ መታወቂያ አገልግሎት
7. ኢትየጵያ ፖስታ፡- ፖስታ አገልግሎት፣ ብሄራዊ መታወቂያ አገልግሎት በድምሩ 2 አገልግሎቶች
8. የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፡- በ5 ቀናት አስቸኳይ ፓስፖርት እድሳት አገልግሎት፣ ጉዳት የደረሰባቸዉ እና ስህተት ያለባቸዉ ፓስፖርቶች አስቸኳይ ምትክ ፓስፖርት መስጠት አገልግሎት፣ ለጠፉና ለተሰረቁ ፓስፖርቶች አስቸኳይ ምትክ ፓስፖርት የመስጠት አገልግሎት ፣ ገፁ ያለቀ ፓስፖርት ዕድሳት አገልግሎት በድምሩ 4 አገልግሎቶች
በአጠቃላይ በማዕከሉ የ8 ተቋማት 27 አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ታግዘዉ እየተሰጡ ሲሆን በጨማሪም ከሌሎች ተቋማትም ተገልጋይ የሚበዛባቸዉ፣የተገልጋይ ቅሬታ ያለባቸዉን፣በክልል ማዕከል የሚሰጡ፣በቴክኖሎጂ ተሳስረዉ መሰጠት የሚችሉ አገልግሎቶችን በመለየት ወደ ማእከሉ ለማስገባት ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸዉ፡፡በመሆኑም ተገልጋዮች ወደማዕከሉ በመምጣት ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን፡፡ ልህቀት በሰዉ ተኮር አገልግሎት!!