በአገልጋይነት ሰሜት ህዝቡን በማገልገል የህብረተሰቡን የአኗኗር ስርዓት መቀየር ይገባል- ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ (ሆሳዕና፣ ታህሳስ 9/2017) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለ702 የቀበሌ ስራ አስኪያጆች "የመልካም አስተዳደር እምርታ በቀበሌ" በሚል መሪ ቃል የአቅም ግንባታ ስልጠና በዋቸሞ ዩንቨርሲቲ ግቢ መሰጠት ጀመረ። በማስጀመሪያው መርሃ ግብር ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በአገልጋይነት ስሜት በመሰጠት ህዝብን ማገልገል ይገባል ብለዋል። የገጠር ማህበረሰብ የኢኮኖሚ ብዝሃነትን በማረጋገጥና የማህበረሰብ የስራ ባህል በማሻሻል የገጠር ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ የቀበሌ ስራ አስኪያጅ ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። የህብረተሰቡን የአኗኗር ስርዓት በመቀየር የክልሉን ህዝብ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚሰጡ የክህሎት ስልጠናዎችን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል። የክልሉ አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብላቱ ስልጠናው በክልሉ የተጀመረውን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ የጎላ ነው ብለዋል። አካዳሚው በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ፈች ጥናት በማድረግ በየደረጃው ላሉ አመራሮች እና ፈፃሚዎች ችግር ፈች ስልጠና እንደሚጥ አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል። ለቀበሌ ስራ አስኪያጆች የሚሰጠው ስልጠናም በመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የአገልጋይ መሪነት፣ መረጃ አያያዝና ማዘመን ርዕሶች ላይ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል። የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማሻሻል ስልጠናው ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። በተሰማራንበት መስክ ሁሉ አገልግሎት አሰጣጣችንን በማሻሻል የህዝቡን እርካታ ማረጋገጥ ይገባናል ብለዋል። ስልጠናው ለተከታታይ 3 ቀን የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል። በመርሃ ግብሩ የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳዊት ሀዬሶን ጨምሮ የክልልና የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።