Skip to main content

ተቋማዊ ለውጥና አቅም ግንባታ ዘርፍ

የማስፈጸም አቅም ግንባታ መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ ተገንዝቦ ተቋማዊ አቅም የገነቡ የመንግስት ተቋማትን ለማፍራት የሚያስችል ስትራቴጂክ  የለውጥ አቅጣጫዎችን፣ ሂደቶችን እና ውጤቶችን በጥልቀት ለመመልከት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ ፕሮግራሞችና ስትራቴጂዎች መሰረት ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለውጥ ማለት የነበረውን አመለካከት፣ አኗኗር እና የአሰራር ዘይቤ ወደ አዲስ ሁለንተናዊ አስተሳሰብና  ተግባር የምንሸጋገርበት እንዲሁም  ለመድነውና ከያዝነው አስተሳሰብና ተግባር አስቀድሞ ባለን መረጃና መረጃው በሚፈጥርብን ፍላጎት ወይም በሚያጋጥመን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ችግር የተነሳ ወደ አልተለመደና ምናልባትም ወደ አዲስ አስተሳሰብና አሰራር የምንሸጋገርበት ሂደት ነው፡፡ 

የለውጥ ሂደት ከግለሰብ እስከ ተቋም፣ ከአገር እስከ አህጉርና ብሎም እስከምንኖርባት ዓለም ድረስ የማይዳስሰው/የማይነካው ክፍል የለም፡፡ በዚህ ረገድ በለውጥ ሂደት ውስጥ ከሚያልፉት መካከል መንግስታዊም ሆኑ የግል ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ተቋማት በለውጥ ሂደት ውስጥ እንዲያልፉ ከሚያደርጓቸው መሠረታዊ ምክንያቶች መካከል የተገልጋዮች ፍላጎትና ምርጫ መለዋወጥ፣ የቴክኖሎጂ ለውጥ፣ በተቋማት መካከል ባለ ሁለንተናዊ የውድድር ይዘት መለዋወጥ ወይም በሌሎች ከተቋሙ ቁጥጥር ውጭ በሆኑ ሌሎች ሁኔታዎች ምክንያት በሚመጡ አስገዳጅ ክስተቶች የተነሳ ነው፡፡

የተቋማት የረጅም ጊዜ ስኬታማነት ምስጢር የሚመነጨው ለተቋማዊ ሪፎርም ካለው ዝግጁነትና ከለውጥ ጋር እራሱን እያጣጣመ ከመሄድ ብቃቱ ጋር ነው፡፡ ከተቋሙ ውስጥም ሆነ ውጭ ለሚከሰት የሪፎርም ፍላጎት ፈጣን ምላሽ በመስጠትና ጊዜው ከሚፈልገው አዲስ አሰራር ጋር ፈጥኖ መላመድ ለተቋሙ ስኬታማነትና ዘላቂነት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ አንድ ተቋም ምንም ያህል ውጤታማ ቢሆንና በጠንካራነቱም የሚወዳደረው ባይኖርም እንኳን ከነበረው ውጤታማ አፈጻጸም ወደኋላ እንዳይመለስና የነበረውን የተሻለ አፈጻጸም ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ በመሪነት ለመቀጠል እንዲችል እራሱን ለሪፎርም ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም በመነሳት ተቋማት የተገልጋዩን ህብረተሰብ ሁለንተናዊ ፍላጎት ማሟላት እንዲያስችላቸው የተለያዩ የለውጥ ሥራ አመራር መሳሪያዎችን ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም አዲስ አሰራርንና አደረጃጀትን ተግባራዊ በማድረግ ተቋማዊ ለውጥን ዕውን ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ስለዚህ መንግሰት አሁን ላይ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ በማዘጋጀት እና በማጸደቅ የህዝብን ፍላጎትና ጥቅም የማሟላት ተልዕኮ እንዲኖረው፣ ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን አሰራር እንዲሰፍን፣ የዜጎችን የመገልገል መብት የሚያጎላና ሁሉ አቀፍ ተሣትፎን የሚያበረታታ እና ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ እንዲሆን እየተሰራ ነው፡፡

ከፖሊሲው አንፃር የተቋማዊ ለውጥ አስፈላጊነት ተቋማዊ ለውጥ ተልዕኮን በቅልጥፍናና በውጤታማነት ለመፈጸም፣ የተገልጋዮች/ዜጎችን ፍላጎት ለማርካት፣ ተወዳዳሪ ለመሆንና የተቋምን ህልውና ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡እያደገ ለሚሄደው የተገልጋዮች ፍላጎት ምላሽ በመስጠት እርካታን ለማረጋገጥ፣ የተወዳዳሪነት አቅምን ለማጎልበት እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር አብሮ ለመራመድ እንዲቻል ተቋማት በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ ማለፍ ይገባቸዋል፡፡ ከመንግስት ተቋማት አንጻር ሲታይ ተቋማቱ በመንግስት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በውጤታማነት በመፈጸም የዜጎችን የአገልግሎትና የልማት ፍላጎት በመመለስ መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንነሳ አገሪቱን ከነበረችበት የድህነት ችግር በማላቀቅ ልማትን በማፋጠንና፣ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን በማስፈን የህዝቦች ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ መሄድ የመንግስት ቁልፍ አጀንዳ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የመንግስት ፖሊሲ አስፈጻሚ የሆኑት ተቋማት ይህን ትልቅ ተልዕኮ ለማሳካት በአደረጃጀታቸው፣ አሰራራቸውና የሰው ኃይላቸው የተሟላና የማያቋርጥ የመፈጸም አቅም እየገነቡ የሚሄዱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ አቅማቸውን ለማጎልበት በሚያስችል የማቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ ማለፍ አለባቸው፡፡ የተቋማዊ ለውጥ አስፈላጊነትም ከዚህ መሰረታዊ ሀሳብ የሚነሳ ነው፡፡ በመሆኑም የሪፎርም ሥራዎች በባህርያቸው የአንድ ወቅት ሥራ ብቻ ሳይሆኑ በየጊዜው አዳዲስ የሥራ አመራር ፍልስፍና ተከትሎ ቀጣይነት ባለው መልክ እየተሻሻሉ ተግባራዊ የሚደረጉ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የፐብሊክ ሴክተር የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ያሉበት ደረጃ በመዳሰስ እና የለውጥ መሳሪያዎች ያሏቸውን ትስስር በግልጽ በማሳየትና ግንዛቤ በመፍጠር ይበልጥ በማዳበር የሪፎርም ሥራን አጠናክሮ መተግበር አስፈልጓል፡፡